ረቡዕ 4 ሜይ 2016

ያልነገርኩሽ ነገር


ሁለቱም ፍቅር ይይዛቸዋል ተብለው የሚጠረጠሩ
አይነት አይደሉም፡፡ ‘እንዲህ የሚባል ነገር አለ
እንዴ?’ ሊል ይችላል አንዳንድ ሰው፡፡ አዎ እንዲህ
የሚባል ነገር አለ፡፡ ለምሳሌ ፡- “እከሌ እኮ ፍቅር
ይዞታል፡፡” ሲባል” “ተዉት እባካችሁ እሱ ልማዱ
ነው፡፡” የሚል መልስ ይሰማል፡፡ አንዳንዴም፡-
“እከሊት እኮ ፍቅር ያዛት፡፡” ሲባል “እሷን?! እንዴት
ተደርጐ?! እሷ እኮ ጀግና ቢጠበስ አይሸታትም!”
የሚባልላትም አለች፡፡ ሁለቱም “እንዴት ተደርጐ”
የሚባልላቸው ናቸው፤ ግን ሁለቱም እንዴት
ተደርጐዎች ፍቅር ያዛቸው፡፡
ሚና እና ሀሌሉያ ተፋቀሩ፡፡
ይህ የሚና እና የሀሌሉያ እውነተኛ የፍቅር ታሪክ
ነው፡፡
ሚና ፀይም ናት፡፡ ፊቷ ክብ ነው፡፡ ፀጉሯ አጭር ሆኖ
ከርዳዳ ነው፤ በደንብ የማይታይ የተፈጥሮ ስስ ከርል
አለው፡፡ የአይኖቿ ቅዶች ያምራሉ፤ ከአንደበቷ ይልቅ
ብዙ ነገር የምትናገረው በአይኖቿ ነው፤ በአይኖቿ
ማድነቅ - መናቅ፣ መቆጣት - ማባበል፣ መጥራት -
መግፋት፣ ማቀፍ - መገፍተር፣ ማመስገን -
ማንኳሰስ…በአይኖቿ፤ ተራ ስሜቶች አታስተናግድም፡፡
አጭር ናት፤ ግን አያስታውቅባትም፤ የትከሻዋ ቀጥ
ማለት፤ የአካሄዷ ስክነት እና ፍሰት ረዥም
ያስመስላታል፡፡ የቆዳዋ ቀለም ይገርማል፤ ስም
የለውም፤ አንዱ አንዴ “ቀለምሽ…” ብሎ ጀምሮ…ምን
እንደሚል ግራ ገብቶት “ቆቅማ ነው፡፡” ብሏታል፡፡
ከዚያ በኋላ “ቆቅማ ቀለም፡፡” ይሏታል፡፡
ሚና ነፃ፣ ግለኛ እና ምክንያታዊ ሰው ናት፤ ያለ
ምክንያት የምታደርገው አንድም ነገር የለም፤ ሁሉ
ነገሯ በምክንያት እና በእቅድ የተቀነበበ ስለሆነ ሰዎች
ይፈሯታል፡፡ ብዙ ጊዜ ሰዎች የባህሪ ድክመት
ያለባቸውን ሰዎች ባያደንቋቸውም ይወዷቸዋል፤ እንደ
ሚና አይነቶቹን ፍፁማውያኖች ግን ፈጽሞ
አይወዷቸውም፤ ወይ ያከብሯቸዋል ወይ ይፈሯቸዋል፤
ጠና ሲል ይጠሏቸዋል፡፡ ሚናን ብዙዎች ያከብሯታል፤
የሚፈሯትም አሉ፤ የምር የሚጠሏትም ትንሽ
አይባሉም፡፡ ሲወቅሷት፤ ሊያሟት ሲጀምሩ፡- “ሠው፤
ሠው አትሸትም…” ብለው ይጀምራሉ፡፡…
ሀሌሉያ ሰው፣ ሰው ይሸታል፡፡ አልኮል ይወዳል፤
የሚጠጣው ከዊንስተን ቸርችል በላይ ነው፡፡ በሲጋራ
ይመሰጣል፤ ከሲግመንድ ፍሮይድ በላይ ነው
የሚያጨሰው፤ ለማያጨሱ ጓደኞቹ በሲጋራ ጦስ
በመጣ ካንሰር የሞተውን የፍሮይድን አባባል
ይነግራቸዋል ፡- “ሠው ሳያጨስ እንዴት ላለማጨስ
ይወስናል?” ሴቶች ይወዳል፤ ሴቶችም ይወዱታል፤
ሲዘሙት እንደ ንጉስ ሠለሞን ነው፤ አምስት መቶ
ሲደመር እቁባቶች አሉት፡፡ አይፈራም፤ እንደ
ሄምንግዌይ ወንድ ተኩል ነው፡፡ ሙዚቃ ይወዳል፤
ሲደንስ አለም ሁሉ አብሮት ይደንሳል፡፡
ሚናን ለመጀመሪያ ጊዜ ያያት እሱ በሚያስተምርበት
ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ለመምህርነት ቅጥር ለቃለ
መጠይቅ ቀርባ ነው፡፡ የቅጥር ኮሚቴ ውስጥ
ነበረበት፤ ቃለ መጠይቅ ከሚያደርጉ አራት ሰዎች
አንዱ እሱ ነበር፡፡ ጥያቄዎቹ ተደጋጋሚ ስለነበሩ እና
ተወዳዳሪዎቹም ብዙ ስለነበሩ ሰልችቶት፣ አቋርጦ
ሲጋራ ሊያጨስ ወጣ፤ ሲመለስ ሚና እየተጠየቀች
ደረሰ፡፡ ስታየው ደነገጠች፤ ሲያያት ደነገጠ፡፡
እርጋታዋ ገርሞታል፤ በጣም ተረጋግታ ነው
የምትመልሰው፡፡ ፍርሃትም የለባትም፤ ለመመሰጥም
አትሞክርም፤ ትጠየቃለች፤ በእርጋታ ትመልሳለች፡፡
“ሚና ጥያቄዎቻችን አልቀዋል፤ እናመሰግናለን፤
ውጤቱን ደውለን እናሳውቅሻለን፡፡” አለ የኮሚቴው
ሰብሳቢ፡፡
“ቆይ፤ ቆይ እኔ አንድ ጥያቄ አለኝ፤ ለሚና፡፡” አለ
ሀሌሉያ፡፡
“ጥሩ እንግዲህ፡፡” አለ የቅጥር የኮሚቴው ሰብሳቢ፤
በቅሬታ፡፡
“ሚና?”
“እህ?”
“የወንድ ተማሪሽ የፍቅር ጥያቄ ቢያቀርብልሽ ምን
ታደርጊያለሽ?”
ያልተጠበቀ ጥያቄ ነበር፡፡ መገረም እና ፈገግታ
ሰፈነ፡፡ ሁሉም የሚናን መልስ እየጠበቁ ነው፡፡
ከረዥም ፀጥታ በኋላ፤
“የወንድ ተማሪዬ የፍቅር ጥያቄ ቢያቀርብልኝ ምን
አደርጋለሁ ነው አይደል ጥያቄው?”
“አዎ፡፡” አሉ አራቱም አንድ ላይ፡፡
“በመጀመሪያ ጆሮውን እቆነጥጠዋለሁ፡፡” ሁሉም
ሳቁ፡፡
“እሺ ከዛስ?” አላት ሀሌሉያ ሲስቅ ያነባውን እንባ
ከአይኑ እየጠረገ፡፡
“ከዚያ ባልቆነጠጥኩት ጆሮው በኩል አርፎ እንዲማር
እነግረዋለሁ፡፡” ሳቅ፡፡
አሁን ሚና የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የህግ የትምህርት
ክፍልን ተቀላቅላ የመምህር ሀሌሉያ የስራ ባልደረባ
ሆናለች፡፡ ሚና ስትቀጠር ሀሌሉያ ካቀረበላት አስቂኝ
ጥያቄ ወዲህ አውርተው አያውቁም፡፡ ያኔ መጠየቅ
የፈለገው ጥያቄ “ተማሪሽ የፍቅር ጥያቄ
ቢያቀርብልሽ መልስሽ ምን ይሆናል?” ሳይሆን “የስራ
ባልደረባሽ የፍቅር ጥያቄ…” እንደሱም አይደለም፡፡
መጠየቅ የፈለገው “እኔ፣ ሀሌሉያ የፍቅር ጥያቄ
ባቀርብልሽ መልስሽ ምን ይሆናል?” ብሎ ነው፡፡
ሁለቱም ተግባብተዋል፤ ሁለቱም ተዋደዋል፡፡
እሷ “ሀሌሉያ የፍቅር ጥያቄ ቢያቀርብልኝ፤ በሀሴት
ይህን ጥያቄ ያቀረበውን አፉን ድብን አድርጌ
እስመዋለሁ፡፡” ብትለው ነበር ፍላጐቷ፤ ግን -
“ጆሮውን እቆነጥጠዋለሁ፡፡” ብላ አሾፈችበት፡፡
የሚገርመው ይህን መልሷን ሲሰማ ሀሌሉያ እየሳቀ
በግራ እጁ፤ ቀኝ ጆሮውን ሲያሽ ነበር፡፡ ይህ ፍቅር
ይሉት ነገር ሁሌ ይገርማል፡፡ ሁለቱም ልጆች በዚያ
ቅጽበት ተዋደዋል፤ በጣም የሚገርመው ደግሞ
እንደተዋደዱ ማወቃቸው ነው፡፡ ብዙ ጊዜ በመጀመሪያ
እይታ የሚከሰት ፍቅር ጣዕሙም፤ ጥልቀቱም፤
እርቀቱም፣ አንደኛ ነው፡፡ ከመላመድ የሚመጣ
ፍቅር፣ ፍቅር አይደለም፤ ኑሮ ነው፡፡
ሚና ሥራ ከጀመረችበት ቀን አንስታ ተስፋ ነበራት፡፡
ይህ ዋዘኛ የስራ ባልደረባዋ አንድ ቀን፣ በቅርብ ቀን
ጥያቄውን እንደሚያቀርብላት እርግጠኛ ነበረች፡፡
እንዲያውም መልሷን አዘጋጅታለች፤ ምን እንደምትል
ብቻ ሳይሆን እንዴት እንደምትለውም ተለማምዳለች፤
ግን ብትጠብቅ፤ ብትጠብቅ፤ ብትጠብቅ…ምንም
የለም፡፡ ሀሌሉያ ካለችበት አካባቢ ግን ጠፍቶ
አያውቅም፡፡ ከእለት፤ እለት እየወደዳት ነው፡፡…
እየወደዳት በመጣ ቁጥር፤ ፍርሃቱም እየጨመረ
መጣ፡፡ ሠላም እንኳ መባባል ተአምር ሆነበት፤
ሆነባቸው፡፡
የሆነ ቀን እንዲህ ሆኖ ነጋ፡- የሀሌሉያ ቤት በክርክር
ጦፏል፡፡
“ብትጠየቅ ምን አባቷ ታመጣለች?”
“ምንም!”
“እና ታዲያ?!”
“መጠየቅ ነዋ!”
“መቼ?!”
“ዛሬውኑ!”
ሀሌሉያ ነው ከራሱ ጋር እየተነታረከ ያለው፡፡
“ምንም”፤ “መጠየቅ ነዋ”፣ “ዛሬውኑ”
የሚሉት መልሶቹ ጠንካሮች አልነበሩም፤
ሲደጋግማቸው ካሰባቸው በላይ ጠነከሩለት፡፡ የዚያን
ቀን እንደሚያወራት ወሰነ፡፡
በባህር ዳር ጫፍ አንደኛው ቤት ደግሞ አንዲት
ቆቅማ ቀለም ያላት ልጅ ንጋቷን እንዲህ እያሰበች
ጀመረች፡፡
“…ለምንም አይደለም የምፈልገው፤ በቃ ጓደኛዬ
ቢሆን ምን ችግር አለው? ደግሞም እኔ
ለከተማውም፤ ለሥራውም አዲስ ነኝ፤ እሱ
አይደለም፤ አንዳንድ ነገሮች ሊረዳኝ ይችላል፤…
ሠላም እለዋለሁ…ከዚያ ሻይ ብንጠጣስ? እለዋለሁ…
ከዚያ ሻይ እየጠጣን ጐበዝ አስተማሪ እንደሆነ
መስማቴን እነግረዋለሁ…አይ እንደሱ አይደለም…
እንዴት ነው ታዲያ?...ለማዋራት የሚከብድ ልጅ
አይደለም…ታዲያ ለምንድነው እኔን የማያዋራኝ
ግን?...ቆይ ሻይ እንጠጣ እለዋለሁ…እንደዚያ ማለት
ችግር አለው?...የለውም…ምን ችግር
አለው?...ከዚያ ሻይ እየጠጣን ጐበዝ አስተማሪ
እንደሆነ መስማቴን እነግረዋለሁ…ከዚያ ለምን ብዙ
እንደሚያጨስ፣ ለምን ከሰኞ እስከ ሰኞ እንደሚጠጣ፣
…ለምን፣ ለምን፣…ለምን እንደሚሸረሙጥ
እጠይቀዋለሁ…ምን አገባሽ? ቢለኝስ? ይለኛል
ደግሞ! ግን ዝሙት ደግሞ ሀጢአት ነው፤ እና የሱ
ነፍስ ገሃነም ውስጥ ብትቃጠል ማን ይጠቀማል?
ማንም…ስለዚህ …ማናገር አለብኝ፤ ዛሬ
አናግረዋለሁ…”
እዚህ ሀሳቧ ጋ ስለሀሌሉያ የሰማችው የማይታመን
ነገር ትዝ አላት፡፡ የህግ ትምህርት ክፍል ሀላፊው፤
ዲኑ፤ የአስተዳደር እና የአካዳሚክ ምክትል
ፕሬዚደንቶች እና የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት
ተሰብስበው፤ “ባስቸኳይ ትፈለጋለህ…” ብለው
ደወሉለት…ሄደ፡፡
“ከሴት ተማሪዎች ጋር ያለህ ቅርበት ጤናማ
አይደለም!”
“ጤናማ ነው፡፡” ነገሩ ወዲያው ነው የገባው፡፡ “ደደብ
ሁላ” አለ በሀሳቡ፡፡
“በጣም ትቀርባቸዋለህ ነው የሚባለው!”
“ብዙዎቹን እንዲያውም ተኝቼያቸዋለሁ፡፡”
“ምን!?”
“ከወደድኳቸው እና ከፈቀዱኝ ሴት ተማሪዎች ጋር
ሁሉ ተኝቻለሁ፡፡”
“ይህ እኮ ለጆሮ የሚከብድ፣ ለጆሮ የሚቀፍ
የዲሲፕሊን ጥሰት ነው፡፡”
“አይደለም፡፡”
“ነው !!!!” እያንዳንዱ ቃለ - አጋኖ አራቱን
ተሰብሳቢዎች ነው የሚወክለው፡፡
“ቆይ አንድ ጥያቄ አለኝ፤ አንድ መምህር ከሴት
ተማሪው ጋር አይተኛ የሚባለው ለምንድነው?”
አሁን ሁሉም ግራ ተጋቡ፡፡ ጥያቄውን አስበውበት
አያውቁም፡፡ ጉዳዩን ብዙ ያሰቡበት፣ ጠልቀው
የሚያውቁት ይመስላቸው ነበር ግን፤ አሁን ጥያቄውን
ይዘው ጭንቅላታቸው ውስጥ መልስ ቢፈልጉ ምንም
የለም፡፡
“ቆይ እኔ እነግራችኋለሁ፤ አንድ መምህር ከተማሪው
ጋር እንዳይተኛ የሚፈለገው፤ ልጅቷን ሲወዳት
እንዳይጠቅማት፣ ሲጠላትም እንዳይጐዳት ነው፤
በትምህርቷ፡፡ አንድ መምህር የወደዳት ተማሪ እሺ
ስትለው የማይገቡትን ጥሩ ውጤት ካልሰጣት፤
ወይም እምቢ ስትለው የሚገባትን እስካልነፈጋት
ድረስ አስተማሪ ከተማሪው ጋር እንዳይተኛ ሊያሳምን
የሚችል ምንም አይነት መከራከሪያ አይኖርም፤ እኔ
ደግሞ ሁለቱን፣ ምን ሁለቱን ብቻ ምንም አይነት
ስህተት ሳልፈጽም ነው ከወደድኳቸው እና ከፈቀዱኝ
ተማሪዎች ጋር የምተኛው፤ ይሄን ሁሉም ያውቃል፡፡”
ይሄን ሁሉም ያውቃሉ፤ አራቱም በየተራ ተያዩ፡፡
ከአራቱ ሶስቱ፣ ማለት ከህግ ትምህርት ክፍል
ሃላፊው በቀር ፕሬዚደንቱ እና ሁለቱ ምክትል
ፕሬዚደንቶች ያገቡት ተማሪዎቻቸውን ነው፡፡
“አንዴ ውጭ ቆየን፡፡” አለው ፊተ ረዥሙ፣ ጀልጋጋው፣
እና አመዳሙ፣ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚደንት፡፡
ሀሌሉያ ወጥቶ፣ ሲጋራውን እያጨሰ፣ ጥሏቸው
በዚያው ወደ ቤቱ ሄደ፡፡ ሁሉ ነገር በዚሁ አበቃ፡፡
“ለምን ታመነዝራለህ?” ብላ ልትመክረው የከጀለችው
ሚና፤ ይህን ስታስብ ተደነቀች፡፡ “ለምን ግን ከሥራው
አላባረሩትም እስከዛሬ?” አለች ለራሷ፣ ደስ የሚል
ፈገግታ ፊቷ ላይ አብርታ፡፡ “ጉድ የሆነ ሰው ነው!”
አለች፤ “ሰይጣን ነው!” አለች አሁንም፤ ሁለመናዋ
እየሳቀ፡፡
በዚያን ቀን ሚና፤ ሀሌሉያ ይወድልኛል ብላ
ያሰበችውን ልብስ ለብሳ ከቤቷ ወጣች፡፡ ሀሌሉያ፤
ሚና ትወድልኛለች ብሎ ያሰበውን ሙሉ ጥቁር ሱፍ
ልብስ እና ነጭ ሸሚዝ በጠዋት ወጥቶ ገዛ፤ ሙሉ
ሱፍ ልብስ ኖሮት አያውቅም፡፡ ሚና የምታዘወትረውን
ቤት ያውቃል፤ ወደ ስራ ከመሄዷ በፊት ቡናዋን
የምትጠጣው ፓፒረስ ሆቴል ነው፤ ከስራ መልስም
ቡናዋን እየጠጣች ከቦርሳዋ የማይጠፋውን መጽሐፍ
ቅዱስ የምታነበው፣ ከቦርሳዋ የማይጠፋው
ማስታወሻ ደብተር ላይ ግጥሞች የምትሞጫጭረው
ፓፒረስ ሆቴል ነው፡፡ ሀሌሉያ ቀን ቡናውን፣ ማታ
ቢራውን የሚጠጣው ክላሲክ የምትባል ቤት ነው፡፡
እሷም እንደዛተችው፤(“ዛሬማ አናግረዋለሁ…”)
እሱም እንደፎከረው ምንም አታመጣም፤ ዛሬውኑ
ምን መጠየቅ) እሱ እሷን ፍለጋ ወደ ፓፒረስ ሆቴል
ሲሄድ፣ እሷ እሱን ፍለጋ ወደ ክላሲክ ባር ስትሄድ
መንገድ ላይ ተገናኙ፤ ጊዮን ሆቴል ጋ ተገናኙ፡፡
ሁለቱም ሁሉ ነገር በግልጽ ታውቋቸዋል፡፡ ፍቅር
እንደዚህ ነው፡፡ ሚና፣ ሀሌሉያ እሷን ፍለጋ እየመጣ
እንደሆነ አውቃለች፡፡ ሱፍ ለብሶ አይታው አታውቅም፤
“እስኪ አሁን ምን ሱፍ የሚያስለብስ ነገር መጣ?”
ሀሌሉያም ሚና እሱን ፍለጋ ወደ ክላሲክ እየመጣች
እንደሆነ ገብቶታል፡፡ “ቆይ እስኪ አሁን በአዘቦት ቀን
ፀጉር ላይ ጽጌረዳ አድርጐ መዋብ ምን የሚሉት
ነገር ነው? ደሞ እንዴት፣ እንዴት ሆና ነው
የዘነጠችው?”
ሲገናኙ ምንም አልተፋፈሩም፤ አልተፈራሩም፡፡
“ሀሌሉያ እንዴት ነህ?” አለችው ሚና፡፡
“ታዲያስ ሚና?”
“ሻይ…” አለች እሷ፡፡
“እንጠጣ፡፡” አላት እሱ፡፡
ተያይዘው ጊዮን ሆቴል ገቡ፡፡ ሁለቱም ሻይ አዘዙ፡፡
“ይኸውልህ፣ ያኔ እኔ ለስራ ስወዳደር ከተጠየኳቸው
ጥያቄዎች አንተ የጠየከኝ ጥያቄ እስከዛሬ…” አፍራ
አቋረጠች፡፡
“እኔም ያኔ፣ አንቺ ለስራ ስትወዳደሪ የጠየኩሽን
ጥያቄ ደግሜ ልጠይቅሽ አስቤ፣ አንቺን ፍለጋ ወደ
ፓፒረስ እየመጣሁ ነበር፡፡”
“ያኔ የጠየከኝ ጥያቄ ይገርማል፡፡”
“አይገርምም፡፡”
“ማለቴ ደስ ይላል፡፡”
“መልስሽ ምንድን ነው?”
“ጥያቄው ምን ነበር?”
ሁለቱም ሳቁ፤ በቃ ፍቅረኛሞች ሆኑ፡፡
እስከዛሬ ድረስ ሰዎች ይከራከራሉ፡፡ አንዱ ወገን፡-
“ታውቃለህ ይኼን እብድ፣ ሰካራም እኮ ለፍቅር
የጠየቀችው እሷ ነች፡፡” ይላል፤ ሌላው “ኧረ ባክህ
የመጀመሪያ ቀን እሷን ለማናገር ብቻ ብሎ ሱፍ
የገዛው እሱ ነው፡፡”
“እሷ ናት የጠየቀችው!”
“እሱ ነው የጠየቃት!”
እስከአሁን ሰዎች ይከራከራሉ፡፡
እየተጫወቱ እያለ፡- (አሁን ሀሌሉያ ቢራ ነው እየጠጣ
ያለው፤ ምን ቢሆን ቆንጆ ነው? ሚናም እሱን አይታ
ጠጥታ የማታውቀውን ቢራ አዛለች፤ ይገርማል፤
ጠጣችው፤ አልመረራትም፤ ይሄም ይገርማል፡፡)
“ምን አይነት ሴት ነው ግን የምትወደው?” አለች
ሚና፤ ሁለተኛውን ቢራ ካጋመሰች በኋላ፡፡
“ሴቶች በሚለው ይስተካከልልኝ፡፡”
“እንዳሉት ይሁን፤ ተስተካክሏል፡፡”
“ሶስት አይነት ሴቶች ነው የምፈልገው፤ አንድ ሚስቴ
የምትሆን፣ ድል ባለ ሠርግ የማገባት፣ ብር አምባር
ሰበረልዎ የማስብልላት፣ የእናትነት ባህሪ ያላት፣
የልጆቼ እናት የምትሆን፣ ልጆቼን ጡት አጥብታ፣ በስነ
- ምግባር አንፃ የምታሳድግ፤ ሽሮ ወጧ ጣት
የሚያስቆረጥም፤ ሸሚዜን የምትተኩስልኝ፣ ከረባቴን
የምታስርልኝ፣ የቤቴ እመቤት…ይህቺ ዋነኛዋ ናት፡፡
ሁለተኛዋ ሴት አንደኛ ደረጃ ጭንቅላት ያላት መሆን
አለባት፤ ኢንተለክቹዋል መሆን አለባት፤ ይኺችኛዋ
ፊልም፣ ትያትር፣ ስዕል አብራኝ የምታይ ናት፤ እና
አይታ የምታደንቅ፣ የምትተች፣ የምትንቅ ሙዚቃ
ሰምታ የምታደንቅ ወይም የምትንቅ፣ በሙዚቃ
የምትደንስ፤ ስለ ደስቶይቭስኪ፣ ስለ ክርስቶስ፣ ስለ
ክርስቶስ ሰምራ፣ ስለ ሶቅራጦስ፣ ስለ ቡድሃ፣ ስለ
ኒቼ፣ ስለ ቶሪዮ፣ ስለ ሮበርት ፒርሲግ፣ ስለ አየን
ራንድ…የምታወራኝ…ጂን የሚጠጣ፣ በሲጋራ
የምትመሰጥ፣…ሶስተኛዋ የምፈልጋት ሴት ምን
አይነት መሰለችሽ ባለጌ የሆነች ሴት፤ አልጋ ላይ
ሁሉን የምትሆን፣ የባለጌዎች አለቃ የሆነች፣ አልጋ
ላይ ሚስቴን የማልጠይቀውን ሁሉ የምጠይቃት፤ እና
ለዚሁ ጉዳይ ብቻ የምንፈላለግ…እ…ለጊዜው ሶስቱን
ካገኘሁ ይበቃኛል፡፡”
“እኔ ሶስቱንም አሟላለሁ፡፡” አለች ሚና፤ በችኮለ ግን
በእርግጠኝነት፡፡ “እኔ ሶስቱንም መሆን፣ ማሟላት
እችላለሁ I am all in one፤ እናት፣ ሀሳቢ፣ እና
“ባለጌ” አይደል ያልከው? እኔ ሶስቱንም መሆን
እችላለሁ፡፡”
“ለዚያ አይደል እንዴ ታዲያ የወደድኩሽ፡፡”
“እንዴት አወቅህ? ሶስቱንም ሴቶች ማለት እናት፣
ሃሳቢ፣ እና “ባለጌ” መሆን እንደምችል እንዴት
አወቅህ?”
“ውቃቢዬ፣ ቆሌዬ፤ ቀልቤ ነገረኝ፡፡”
“ስለ እናት ያልከው…ስለ ሶስቱም ሴቶች ያልከው ደስ
ይላል፡፡ ከሁሉም ግን የቷ ትበልጥብሃለች?”
“እናት የሆነችዋ ናታ፤ ብዬሻለሁ እኮ ዋነኛዋ እሷ
ናት፡፡”
“ለምን”
“አንዴ አንዲት ሴት ሳደንቅ ምን እንዳልኩ
ታውቂያለሽ? ልንገርሽ፤ “የልጆቼን ነፍስ በእሷ እጅ
አምናለሁ” አልኩ፡፡ እንዲህ ያስባለችኝ ሴት የጓደኛዬ
ሚስት ባትሆን ኖሮ ልወዳት ምንም ጉዳይ ነበርኩ፡፡”
“እኔ ስለራሴ ሰው ጠይቄ አላውቅም፤ አንተ ግን ስለ
እኔ ስለምታስበው እጨነቃለሁ፤ ማወቅ እፈልጋለሁ፤
በጣም ስለወደድኩህ ይመስለኛል፡፡ እንዳትታዘበኝ፤
ምን አይነት ሰው አድርገህ ነው የምታስበኝ?”
“እሚገርምሽ እኔም ስለ እራሴ ተመሳሳይ ጥያቄ
ልጠይቅሽ ነበር፡፡ ጥያቄውን ካነሳሽ አይቀር ልንገርሽ፤
አንቺ አብርሃም ነሽ፡፡”
“ምን?!” ግራ ተጋብታለች፡፡
“ይህን ነገር አታውቂም?”
“ምኑን?!”
“ይኼውልሽ ሰዎችን ሁሉ በባህሪ ብንከፍላቸው
በአራት ምድብ ይወድቃሉ፤ ወይ አብርሃም ወይ ሙሴ
ወይ ጳውሎስ ወይ ጴጥሮስ ናቸው፡፡ የጥንት ምድብ
ነው፡፡ ሄፓክራተስ ነው በመጀመሪያ ምድቡን
ያወጣው፡፡ ሳይኪያትሪስቶች ለህክምና፣ ፀሐፊዎች
ለገፀ ባህሪ ቀረፃ የሚጠቀሙበት የባህሪ ጐራ
ድልድል ነው፡፡”
እንዲህ ብሉይ የሆነ የባህሪ ምድብ አለማወቋ
አናዷታል፡፡
“ሄፓክራተስ ከክርስቶስ ልደት በፊት አይደል የኖረው?
ስለጴጥሮስ እና ጳውሎስ ምን ያውቃል?” አለች
አለማወቋ ያላናደዳት እየመሰለች፡፡
“አይ እሱ ባህሪያቱን የከፋፈለው phlegmatic,
melancholic, choleric እና sanguine ብሎ
ነው፤ በጥቅሉ The four Temperaments ነው
የሚባሉት፤ በኋላ የመጡ አዋቂዎች ብዙዎች በቀላሉ
እንዲረዱዋቸው ብለው አብርሃም፣ ሙሴ፣ ጳውሎስ
እና ጴጥሮስ ብለው ከፋፈሏቸው፤ እንደ የባህሪው
ዝርዝር አይነት፡፡”
“አብርሃም ቁጥብ፣ ጥንቁቅ፣ ሃሳብ የሚያዘውትር፣
ሠላማዊ፣ ራሱን የሚገዛ፣ እምነት የሚጣልበት፣
ባህሪው የማይዋዥቅ እና ጭምት ነው፡፡”
ፊቷ ፈካ፡፡
“እኔም ይሁን ሁሉ ነኝ?!”
“በተጨማሪም ውብ ነሽ፡፡”
ልትስመው ከጅላለች፤ ሊስማት ፈልጓል፡፡ ሁለቱም
አፈሩ፡፡
“አንተስ ማነህ? አብርሃም፣ ሙሴ፣ ጳውሎስ ወይስ
ጴጥሮስ?”
“ገምቺ፡፡”
“እምቢየው፣ እራስህ ንገረኝ!”
“የኔ ለየት ይላል፤ እኔ የሙሴ እና የጳውሎስ ቅይጥ
ነኝ፤ እኔ እንደ ሙሴ ጭንቀታም ነኝ፤ አይታወቅብኝም
እንጂ ጭንቀታም ነኝ፤ እናም የሚገርምሽ አሁንም
አይታወቅብኝም እንጂ እንደ ሙሴ ግትር እና
ጨለምተኛ ነኝ፤ እነዚህ የማይታወቁ ድብቅ
ባህሪያቶቼ ናቸው፡፡
በተረፈ እንደ ጳውሎስ ስሜታዊ፣ እረፍት የለሽ፣
ሀይለኛ፣ በቀልቤ የምመራ፣ ቀልጣፋ እና ንቁ ነኝ፡፡ …
እንደ አንቺ የአብርሃም አይነት ባህሪያት ያሉዋቸው
ሰዎች ወይም አብርሃሞች ጥሩ ሀኪሞች፣ የማይረቱ
ጠብቆች፣ የሚደመጡ ሸምጋዮች እና ዲፕሎማቶች፣
ምርጥ ፀሀፍት፣ ወደር የሌላቸው መምህራን፣
ይሆናሉ፤ በጣም ይገርማል፤ የአንቺን አሁን
ተመልከቺ፤ የተማርሽው ህግ፣ የመረጥሽው ሙያ
ደግሞ መምህርነት ነው፤ ትምህርትሽን በጥሩ
ውጤት ነው ያጠናቀቅሽው፤ አሪፍ መምህር
እንደምትሆኚ ደግሞ አልጠራጠርም”
“አመሰግናለሁ፤ ትገርማለህ፤ እራስህንም ሠዎችንም
በደንብ ታውቃለህ”
“ይኼውልሽ ለኔ የሰው ዘር የተረገመው ቀፋፊው
እርግማን ጥረህ፣ ግረህ፣ በላብህ ወዝ ኑር የሚለው
ሳይሆን ጥረህ ግረህ እራስህን ፈልገህ እጣ
ይመስለኛል፡፡” ሁለቱም በቀልዱ ሳቁ፡፡
የዚያን ቀን የጊዮን ውሎአቸው ይኸው ነበር፡፡
ፍቅር አሀዱ ተባለ፡፡
ሀሌሉያ ሚናን እንዳፈቀረው አፍቅሮ አያውቅም፤ ኧረ
እሱ ጭራሽ አፍቅሮ አያውቅም፤ አሁን ግን
የሚያስበው ስለ ፍቅር፣ የሚያነበው ስለ ፍቅር፣
የሚያደምጠው የፍቅር ሙዚቃ ነው፡፡ በየቀኑ
ከሚሰማቸው የፍቅር ዘፈኖች የወደዳቸውን ሀረጎች
ስንኞች እየፃፈ ለሚና ስልኳ ላይ ይልክላታል።
የትኛውም ሀረግ፣ የትኛውም ስንኝ ግን እንደልቡ
አልሆነለትም፣ ግን ዝም ከማለት ይሻላሉ ብሏል፡፡
ከሚልክላት እያንዳንዱ መልእክት ሥር እንዲህ
የሚል ሀረግ ያክልበታል፡፡ “ግን ያልነገርኩሽ ነገር
አለ፡፡”
“ከወደድኩሽ በላይ ወደድኩሽ መልሼ …”
(ግን አንድ ያልነገርኩሽ ነገር አለ)
“Truly, Deeply, Madly …”
(ግን አንድ ያልነገርኩሽ ነገር አለ)
መውደዴን ወድጄዋለሁ …”
(ግን አንድ ያልነገርኩሽ ነገር አለ)
“I love you eight days a week …”
(ግን አንድ ያልነገርኩሽ ነገር አለ…)
Said I love you but I lied, cause this is
more than love I feel inside.
(ግን አንድ ያልነገርኩሽ ነገር አለ)
(ሀሌሉያ ከላይ የተጠቀሱትን ሀረጎች የወሰዳቸው፣
በቅደም ተከተል፡- ከጥላሁን ገሰሰ፣ ከሳቬጅ ጋርደን፣
ከዳዊት መለሰ፣ ከዘ ቢትልስ፣ ከቴዎድሮስ ካሳሁን፣
ከማይክል ቦልተን የፍቅር ዘፈኖች ነው፡- ደራሲው፡፡)
ግን አንድ ያልነገርኩሽ ነገር አለ የሚለው ያልነገራት
ነገር ኖሮ አይደለም፤ ሁሉን ነገር ነግሯታል፤ ግን
ቢነግራት፣ ቢነግራት፣ አልጠግብ ያለው …
እንደሚወዳት ነው፤ እና አንድም ቀን እንደሚወዳት
ነግሯት የሚያውቅ አይመስለውም። ደውላ ወይ
አግኝታው፡- “ምንድነው ያልነገርከኝ ነገር?” ብትለው
“እንደምወድሽ ነዋ!” ይላታል፡፡
ኧረ እንደውም ጠይቃዋለች፡-
“ምንድነው ያልነገርከኝ ነገር?!” አለችው አንድ ቀን
ቆጣ ብላ፡፡
“እንደምወድሽ ነግሬሽ አውቃለሁ እንዴ?” አለ
የምሩን፡፡
“አስጠሊታ፤ ያልነገርከኝ ነገር ምንድነው?”
“ምንም ያልነገርኩሽ ነገር የለም፤ የደበቅኩሽ
ምስጢር እንደምወድሽ ብቻ ነው፡፡”
አንድ ቀን፡-
“ከአሁን በኋላ የማንንም ሙዚቃ፣ የማንንም ግጥም
እንድትጋብዘኝ አልፈልግም፣ ከአሁን በኋላ
የምፈልገው የአንተ ቅንብር የሆነ ሙዚቃ፣ የአንተ
ድርሰት የሆነ ግጥም፣ የአንተ ቅብ የሆነ የሥዕል ሥራ
ነው፡፡”
“እሺ እስማማለሁ፤ ግን ለመጨረሻ ጊዜ
የገብረክርስቶስን፣ አንድ ግጥም ልበልልሽ፡፡”
እስከዛሬ የራሱን ገለፃ ተጠቅሞ ፍቅሩን ባለመግለፁ፣
እሷም ይህን አስተውላ በግልፅ በመናገሯ አፈረ፡፡
“ከዚህ በኋላ ያንተ ካልሆነ የሌላ የማንንም
አልፈልግም፡፡”
“መልካም”
የሚወደውን የገብረክርስቶስ ደስታን “ለሚወዱት
ምነው?” የሚለውን ግጥም አለላት፡፡
አንድ ቀን የህግ ትምህርት ክፍል ሀላፊ ሀሌሉያን
አስጠራው፡፡
“ከፕሬዚዳንት ቢሮ አስቸኳይ ደብዳቤ መጥቶ ነበር”
“ምን የሚል?”
“የትምህርት እድል ነው፤ በሲኒየርነትህ እና ባለህ
የትምህርት ዝግጅት ብትወዳደር የምታልፈው አንተ
ነህ፤ ግን ደግሞ ሴቶች ይበረታታሉ ይላል
ደብዳቤው፡፡” አለው፡፡
ወዲያውኑ የሆነ ነገር ብልጭ አለለት፤ ሀሌሉያ፡፡
“እኔ በቅርቡ የመማር ፍላጎት የለኝም፤ ለምን ሚናን
አታናግራትም?” ድምጹ ውስጥ ጥያቄ ሳይሆን ትእዛዝ
አለ፡፡
“እኔም የፈለኩህ ምን እንደምትል ልሰማህ ብዬ ነው”
“የኔን ሰምተሃል፤ ሚናን አናግራት” ትእዛዝ ነው
አሁንም፡፡
የትምህርት እድሉን ሚና አገኘች፤ በስውዲን ሀገር
ለአንድ አመት የሚዘልቅ በሰብአዊ መብት ህግ ላይ
የሚሠጥ ስልጠና ነው፡፡ ሚና ስላገኘችው
የትምህርት ዕድል ስትነግረው፤ ‘Congra’ አላት
አቅፎ፡፡ የትምህርት እድሉን እሱ አሳልፎ እንደሰጣት
አልነገራትም፡፡
ታህሳስ ሀያ ዘጠኝ ቀን የሚና የልደት ቀን ነው፡፡ ጥር
አንድ ቀን ከባህር ዳር አዲስ አበባ፣ ጥር ሁለት ቀን
ደግሞ ከአዲስ አበባ ወደ ስቶክሆልም የምትበርበት
ቀን ነው፡፡
ይህን ድርብ በአል ለማክበር ፓፒረስ ሆቴል
ተቀጣጠሩ፡፡ ሚና የምትወደው ወይ የምታዘወትረው
ጥግ ላይ ተቀመጡ፡፡ ሀሌሉያ ቀደም ብሎ ሁሉ ነገር
እንዲዘጋጅ አዞ ነበር፤ ኬክ፣ ሻማ፣ ሻምፓኝ … ሁሉም
ተዘጋጅቷል፡፡ ሚና ይህን ሁሉ ጠብቃለች፤ ኬክ፣ ሻማ፣
ሻምፓኝ … አለ፤ የምትወደው ሠውዬ ጥቁር ሙሉ
ሱፍ፤ በነጭ ሸሚዝ ለብሷል፤ ለብሶላታል።
አምሮበታል፤ ሚና ግን አንድ ነገር በጉጉት
እየጠበቀች ነው፡፡ በዚህ ቀን ሰውዬው ምን አይነት
ስጦታ እንደሚያበረክትላት ለማየት ጓጉታለች፡፡
እራሷን እስክትታዘብ፣ እስኪያስታውቅባት ድረስ
ተቅበጠበጠች፡፡ ሀሌሉያ እጅ ላይ ደግሞ ምንም
አይነት ለስጦታ የሚሆን ጥቅል አይታይም፡፡ ይበልጥ
ተቅበጠበጠች፡፡ እሷ ለዚህቀ ድንቅ ሠው ዛሬ ልዩ
ስጦታ አዘጋጅታለታለች፡፡ ቀይ ስጦታ፡፡
እሱስ? ያ አይደለ እንዴ ታዲያ ጥያቄው፡፡
“እወድሻለሁ” አላት፡፡
“ቀጣፊ፣ ውሸታም!”
“እንዴት እንደምወድሽ ታውቂያለሽ?” አላት እንዴት
ነው የምትወደኝ? እንድትለው አማልክቶቹን
እየተማፀነ፤ አማልክቶቹ ፀሎቱን ወዲያው ሠሙት፡፡
“እንዴት ነው የምትወደኝ?” አለችው ሚና። ተነስቶ
ቆመ፣ ከኪሱ ወረቀት አወጣ፣ በእርጋታ ዘረጋው፡፡
“ክብርት ሆይ ይህ ግጥም ላንቺ በረከት ይሁን ብዬ
እራሴ የፃፍኩት ነው”
የሚከተለውን ግጥም አነበበላት፡፡
እንዴት ነው የምወድሽ እንኳ?
እንደ አበቦቹ ሽታ፣
እንደ ቢራቢሮ እስክስታ፣
እንደ ጥርኝ ጭቃ፣
ልክ እንደ ስጦታ እቃ፣
እወድሻለሁ እኔ እወድሻለሁኝ፡፡
እንደ ፍልስፍና ሃሳብ፣
ሊጠግብ እንዳለ ረሀብ፣
እንደ ህፃን ልጅ ሳቅ፣
እንደ ዘላለማዊ ሀቅ፣
እወድሻለሁ እኔ፣ እወድሻለሁኝ፡፡
እንደ ሎጂክ፣
እንደ ተፈጥሮ ህግ፣
እንደ ቋንቋ፣
ልክ እንደ ሙሉ ጨረቃ፣
እወድሻለሁ እኔ፣ እወድሻለሁኝ፡፡
እንደ ሙዚቃ ቅንጣት፣
እንደ አልጋ ውስጥ ትኩሳት፣
ልክ እንደ እናቴ ስም፣
እንደ ልጅነቴ ህልም፣
እወድሻለሁ እኔ፣ እወድሻለሁኝ፡፡
እንደ ግጥም ስንኝ፣
አንጀሎ እንደጠረበው ቋጥኝ፣
እንደ ጠዋት እንቅልፍ፣
እንደ አየር ራንድ ፅሁፍ፣
እወድሻለሁኝ እኔ፣ እወድሻለሁኝ፡፡
እንደ ብርቱካን ውሃ፣
እንደ ብርሃን ዘሃ፣
እጄ ላይ እንደያዝኩት ሲጋራ፣
እንደ ቀዝቃዛ ቢራ፣
እንደ ሊዮናርዶ ስራ፣
እወድሻለሁ እኔ፣ እወድሻለሁኝ፡፡
ፍቅሬ ሁሉን እንደ እርሺ
ይህን እንደ ብቻ ያዢ፤
አፈቅርሻለሁ ነፍሴ፣
ልክ እንደ እራሴ፡፡
ልክ አንብቦ እንደጨረሰ አካባቢያቸው በጭብጨባ
ቀለጠ፤ ሁለቱም ደነገጡ፤ የምር ደነገጡ፡፡
ዙሪያቸውን ቢያዩ በቤቱ አስተናጋጆች እና በሆቴሉ ስራ
አስኪያጅ ተከበዋል፡፡
“አንድ ጊዜ …” አለ የፓፒረስ ሥራ አስኪያጅ፡- “አንድ
ጊዜ፣ የሆቴሉ ሠራተኞች ስጦታ ስላዘጋጀንላችሁ
እንድትቀበሉ በላቀ አክብሮት እንጠይቃለን” ድምፁ
ውስጥ ፍቅር ነው ያለው፤ ድምፁ ውስጥ እና አኳኋኑ
ውስጥ ቅርበት አለ፡፡
ብዙ ጊዜ ሚናን እና ሀሌሉያን የሚያስተናግደው ልጅ፣
ኬክ እና ብላክ ሌብል ውስኪ ከጎናቸው ያለው
ጠረጴዛ ላይ አኖረ፡፡ ሀሌሉያ ያዘዘውን ኬክ ሚና
እየተጨበጨበላት “Happy Birthday to Mina”
እየተባለላት ቆረሰችው፡፡ የሆቴሉ ሠራተኞች ለሁለቱ
ያበረከቱትን ኬክ ሀሌሉያ እንዲቆርስ ተጋበዘ፡፡
ከፈተው፡- “ለሚና እና ለቴታ፡- ከፓፒረስ” ይላል፤
ሀሌሉያ ግንባሩን ቅጭም አደረገ፤ ሊና አጠገቡ ናት፤
እሷም እሱን ተከትላ ቅንድቧን ቅጭም አደረገች፡፡
“ቴታ ምን ማለት ነው? ምንድነው?” አሉ ሀሌሉያ እና
ሚና አንድ ላይ፡፡
“Tamed Tiger ማለት ነው፤ ያንተ ቅፅል ስም ነው”
አለች ፊቷ፣ አንገቷ፣ እና እጆቿ በአረንጓዴ የደም
ስሮች የተሞሉ፤ ቀጭን፣ ረዥም፣ ቆንጆ አስተናጋጅ፡፡
ስሙን እሷ እንዳወጣችለት ያስታውቅባታል፡፡
የሬይ ቻርለስ Hallelujah-I Love Her So
የሚለው ዘፈን በሆቴሉ ማጫወቻ እየተጫወተ ሀሌሉያ
ኬኩን ቆረሰ፡፡ የሬይ ቻርለስ ዘፈን ሲያልቅ የቢሊ ኦሽን
Caribbean Queen ቀጠለ፡፡ የሚከተሉትን
ስንኞች፡- “In the blink of an eye I knew her
number and her name; yeah; She Said I
was a Tiger She wanted to tame” ሲሰማ
ፈገግ አለ፤ ሀሌሉያ፡፡ Tamed Tiger ያለችውን
አስተናጋጅ በአይኑ ፈለጋት፤ አገኛት፤ እየሳቀች
አየችው፤ በአይኗ ቀስ ብላ ሳመችው፤ አፈረ፡፡
አሪፍ ፌሽታ ሆነ፡፡
ለሁሉም ከብላክ ሌብሉ ከተቀዳ በኋላ ሀሌሉያ
ውስኪውን ከነጠርሙሱ ያዘው፤ በጠርሙሱ ነበር
የሚጠጣው፡፡ ሚና ሻምፓኙን ተያይዛዋለች፤
በየመሀሉ የሀሌሉያን ጠርሙስ እያነሳች ትጎነጫለች።
ሞቅታ፡፡
ሚና ከዚህ በፊት እንደዚህ አይነት ደስታ ተሰምቷት
አያውቅም፤ ከዚህ የሚልቅ ደስታም አለ ብላ
አታስብም፤ ፍፅምና፣ ፅድቅ፣ ከፍታ፣ ልዕልና፣ … ይህ
ሁሉ ነው የተሠማት፤ እና ለዚህ ሁሉ ደስታ መነሻ
ለሆነው ለአቶ ቴታ፡- “እንዴት ደስ የሚል ቅፅል ስም
ነው ግን? እኔንም እሱንም የሚያወድስ ስም ነው፤
እሱ ነብር ነው፤ የገራሁት ደግሞ እኔ፤ አይ መመፃደቅ
አበዛሁ መሰለኝ፤ እኔ አይደለሁም ፍቅር ነው የገራው፣
እያለች አሰበች፡፡
ለሀሌሉያ፣ ለተገራው ነብር ስጦታ አዘጋጅታለታለች፤
ቀይ ስጦታ፡፡ ዛሬ አብረው ነው የሚያድሩት፤
አልተባባሉም፤ እንዲያ አልተባባሉም፤ አብረን
እናድራለን አልተባባሉም፤ አብረው አድረው
አያውቁም፤ ግን ዛሬ አብረው ያላደሩ መቼ ሊያድሩ
ነው? ዛሬ አብራው ታድር እና ሲነጋ ሴት ሆና
ትነቃለች፡፡ አሪፍ ስጦታ እንደሆነ እርግጠኛ ናት፡፡
እራት አልበሉም ነበር፣ ኬኩን ቀመሡ፣ መጠጡን
አጣጣሙት፤ ሀሌሉያ ድሮም ቢሆን ምግብ ላይ ብዙ
አይደለም፡፡
“እራት ልጋብዝህ፤ ሰመር ላንድ እንሂድ” አለችው፡፡
ሞቅ ብሎታል ቴታ፡፡
ለብቻው ሲያስብ እንዲህ እያለ ነበር፡- እራት? አዎ፤
እርቦኛል፤ ሰመርላንድ? ለምን እዚያ?
“እዚሁ እንብላ!” አላት ድምጽ አውጥቶ፡፡
“አይሆንም፤ ሰመርላንድ ፒዛቸውን ለጉድ ነው
የምወድላቸው” አለችው፡፡
ውሸቷን ነው፣ ከአዲስ አበባ መጀመሪያ ባህር-ዳር
ስትሄድ ያረፈችው ሠመርላንድ ነው፤ መኝታቸውን
ወዳላቸዋለች፡፡
ዛሬም እዚያ ነው ማደር፡፡
ሰመር-ላንድ ሆቴል ሄደው እራታቸውን ፍቅራቸውን
በጉርሻ እየገለፁ፣ በአይኖቻቸው አድናቆት እየተቀባበሉ
በሉ፡፡
እሷ እንዲህ ስትል እያሰበች ነበር፣ “ምናለ፤ ባልጐ
ባያውቅ ኖሮ?! ልክ እሱ ለኔ የመጀመሪያዬ
እንደሆነው ሁሉ፣ እኔም ለሱ የመጀመሪያው ብሆን
ኖሮ እንዴት ድንቅ ይሆን ነበር?! በስመአብ ግን
ከስንቶቹ ጋር ተኝቷል? … ግን ይተኛ፣ ምርጥ ሰው
ነው …”
እሱ በበኩሉ፡- “ቴታ ነው ያሉኝ? ይገርማል … ይህች
ነብስ ነገር የሆነች ልጅ ናት የገራችኝ … ሲከታተሉኝ
ነበር ማለት ነው? ይገርማል፤ ቴታ? … እኔ ደግሞ
ይህቺን ብርሃን የሆነች ልጅ ፊኒክስ ብያታለሁ … እንደ
እሷ አይነት በሺህ አመት አንዴ ነው የሚገኘው …
ለዚያውም ፊኒክሶች አይወልዱም፤ አይወለዱም፤
እራሳቸውን ከራሳቸው ነው የሚፈጥሩት፤ ለዚያውም
በሺህ አመት አንዴ … ሚና ፊኒክስ ናት … አፍቅሬ
አላውቅም ነበር … ፍቅር ይሉት ነገር ግን ደስ
የሚለው ነገር አለው … በተለይ ከእንደዚህች አይነቷ
ጋር ሲሆን የፅድቅ ይሆናል … የዛሬ አመት ከስዊድን
ስትመለስ አለምን በሚያነጋግር ሠርግ አገባታለሁ …
እስከዚያ እጠብቃታለሁ … አቦ እስከዘላለም
እጠብቃታለሁ …”
ግን ገላው ገላዋን ከጅሎ በረሃብ እየተቃጠለ ነው፤
እየነደደ፡፡
“እስከዛሬ ወሲብን አራክሼዋለሁ … አሁን ግን
አልስገበገብም … ፈፅሞ አልስገበገብም …
እጠብቃታለሁ … ስልጠናዋን ጨርሳ ከስቶኮሆልም
ስትመለስ … የሠርግ ዳስ አስጥዬ ነው የምጠብቃት
… ከዚያ ብር አምባር ሰበረለዎ፤ ሆሆ ጀግናው ልጅዎ
… ይባልልናል … አንድ አመት በጣም ቅርብ ነው፣
እጠብቃታለሁ …”
ግን አሁንም ገላው ገላዋን ከጅሎ በረሃብ
እየተቃጠለ ነው፤ እየነደደ፡፡
ሚና በበኩሏ በደስታና በፍርሃት ተውጣለች፡- “…
የመጀመሪያው ቀን እንዴት ይሆን?... እንዴትም ይሁን
… ሀይለኛ ደስታ ሳይኖረው አይቀርም … ደሞ እኮ
ልጁ ሀሌሉያ ነው…”
ሳትነግርው ተነስታ ወደ ሆቴሎ እንግዳ መቀበያ
ሄደች፤ አልጋ ተከራየች፤ በመጀመሪያ ባህር-ዳር
ስትመጣ ያረፈችበትን ክፍል ነው የተከራየችው፤
ክፍል ቁጥር 113፡፡
ሀሌሉያ የሠውነቱን ረሃብ ስላልቻለ አንድ መላ ዘየደ፤
ወደ ቤቱ መሄድ፤ ሄደ፡፡ ወደ ቤቱ እየተንገዳገደ ሲሄድ
በቀስታ እንዲህ እያለ እየዘፈነ ነበር፡-
“… ብር አምባር ሰበረልዎ፣
ብር አምባር ሠበርልዎ
ሆሆ ጀግናው ልጅዎ፤
አለምሽ ዛሬ ነው ዛሬ
ሆሆ! እቴ ሸንኮሬ …”
እዚህ ጋ በሀሳቡ ቆም አለ፡- “…አሃ! አሃ!
በመጀመሪያ በሠርግ ያገባችው ድንግል ሙሽራ
የወይዘሮ ሸንኮሬ ልጅ ነበረች ማለት ነው …?” ከት
ብሎ ሳቀ፡፡ “ይኸው የወይዘሮ ሸንኮሬ ስም እስከዛሬ
ሲጠራ ይኖራል፤ የወይዘሮ ሸንኮሬ ልጅ ስሟ ማን
ነበር ይሆን…? ሚና እንደሚሆን እርግጠኛ ነኝ…”
እንዲህ እያለ ቤቱ ደረሠ፡፡ ቤቱ እንደደረሰ ጫማውን
ብቻ አውልቆ አልጋው ላይ ተዘረረ፤ ወዲያውኑ
እንቅልፍ አቀፈው፡፡
ሚና ስትመለስ ሀሌሉያ የለም፤ መታጠቢያ ቤት ሄዶ
ይሆናል ብላ ጠረጠረች፣ ብትጠብቅም አይመጣም፡፡
ስልኩ ላይ ደወለች፤ ዝግ ነው፡፡
ጥግ ላይ ቆሞ አትኩሮ የሚመለከታትን አስተናጋጅ
ጠራችው፡፡
“እሱስ?!” አለችው፤ ሀሌሉያ ተቀምጦበት የነበረውን
ወንበር እየጠቆመች፡፡
“ሄዷል፤ ሂሳብ ከፍሎ ሄዷል” አነጋገሩ ሀሌሉያን
በደንብ እንደሚያውቀው ያስታውቃል፡፡
አላመነችም፡፡ ካለማመኗ እና ግራ ከመጋባቷ የተነሳ፡-
“እስኪ!” ብላ እጇን ዘረጋች፤ ለአስተጋናጁ
እንዲምልላት፡፡
እጇን ግጥም አድርጐ መታት፤ አመታቱ ያማል።
ስልኩ ላይ ደግማ ደወለች፤ ዝግ ነው፡፡ ዝግ መሆኑን
እያወቀች ደጋግማ ደወለች፡፡ ዝግ ነው!
ሀሌሉያ ትቶት የሄደውን ውስኪ ከነጠርሙሱ አንስታ
አንደቀደቀችው፤ ጠርሙሱ በትንፋሿ ድምፅ
እስኪጮህ ድረስ አንጠፈጠፈችው፡፡ አስተናጋጁ
በቅርብ እርቀት አለ፤ በምልክት ጠራችው፤ ተጠጋት፤
በእጇ ያለውን ቁልፍ አቀበለችው፤ የቁልፉ
ማንጠልጠያ 113 ይላል፡፡
በጥያቄ ዓይን አያት፡፡
“ውሰደኝ” አለችው፡፡ ደጋግፎ አነሳት፡፡ ሠክራለች፤
ሚዛኗን ጠብቃ መቆምም መራመድም አልቻለችም፡፡
ግማሽ አቅፎ፤ ግማሽ ደግፎ ወሰዳት - ወደ 113
ቁጥር፡፡ በአንድ እጁ እሷን ደግፎ በሌላ እጁ የመኝታ
ክፍሉን ቁልፉ ከፈተው፡፡
ይዟት ገባ፡፡
ውስጥ ሲገቡ ከእቅፉ ተላቃ እንደምንም ብላ እራሷን
ችላ ቆመች፤ ቆሞ ያያታል፡፡
“በሩን ዝጋው”
ዘጋው፡፡
“አታፍጥብኝ፤ ና ዚፔን ክፈትልኝ”
ከማጅራቱ እስከ ወገቧ ያለውን የቀሚሷን ዚፕ
ከፈተው፤ እጆቿን ከቀሚሷ ስታወጣ፣ ቀሚሷ መሬት
ወደቀ፤ ቀይ ቀሚስ፡፡
ወደ አስተናጋጁ ዞረች፤ ጡቶቿ፤ እዚህ ጋ አንድ
የሀገሬ ፀሐፊ ያለውን መዋስ ግድ ነው፤ “ጡቶቿ
የመዳይ ክዳን ይመስላሉ”
አስተናጋጁ አፈጠጠባቸው፡፡
“ያዛቸው!” አለችው ሚና፡፡
በቀስታ ያዛቸው፡፡
“በደንብ ያዛቸው”
ጨመቃቸው፡፡
ከዚያ ከንፈር፣ ትንፋሽ፣ ምራቅ፣ ሙቀት፣ ላብ፣
ብርሃን፣ ቃጠሎ፣ ሲቃ፣ ፀጉር፣ ገላ፣ ትኩስ ገላ፣
የሚሞቅ ነገር … ሙቀት፣ ሙቀት ላብ፣ … እሳተ
ገሞራ፣ ህመም፣ ደም … ፍሬ፣ እንቁላል፣ ዘር …
ድካም፡፡
እንቅልፍ፡፡
ተፈፀመ፡፡

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ